ማንኛውም የሚመረጠው አዲስ መንግስት ሀገራችንን ለመጥቀም ካሰበ፤ ያሉብንን ችግሮች በቅደም ተከተል አስቀምጦ፤ በጣም አንገብጋቢ የሚባልውን ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ ቢሰራ፤ ለሀገራችን ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። መቼም ሁላችንም እንደምንረዳው ከተማን ማስዋብም ሆነ አዲስ ቤተ-መንግስት የሚሰራው ኑሮ ሲደላ ነው። ነገር ግን ከነሱ የሚቀድሙ እጅግ በርካታ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉን።
በኔ እይታ በሀገራችን ላይ ያሉት ችግሮች እጅግ በጣም ብዙ ቢሆኑም ጠቅለል አድርገን ካየናቸው በሶስት ልንከፍላቸው እንችላለን
የሰላም እጦት
ሰላም ምን ያህል አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑ የሚታወቀው መጥፋት ሲጀምር ነው። ያለምንም ጭንቀት ልጆችን ማሳደግ፣ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት፣ ሀብት ማፍራት …ወዘተ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።
ሰላም ሲጠፋ
ይህ የተዘረዘረው በትንሹ ከላይ ከላዩ ለማሳየት ነው እንጂ፤ የሰላም እጦት እጅግ ከባድ ነው።
ለሀገራችን ሰላም ማጣት በርካታ መንስኤዎችን መዘርዘር ይቻላል ነገር ግን በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ አራት ምክንያቶች እነዚህ ናቸው ፦
መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን ያልመለሰ ሕገ-መንግስት መኖሩ ወይም ሕገ-መንግስቱ መለወጥ አለበት ብሎ የሚያምን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ መኖሩ፤ ለሰላማችን መደፍረስ ዋነኛ ተጠያቂ ነው።
አስተዳደራዊ ተንኮሎች እና የአንዳንድ ኃይሎች የበላይ የመሆን ፍላጎቶች ሰላምን ለማደፍረስ ከፍተኛ አስትዋጽዖ ያደርጋሉ። በአስተዳደር በተለያየ እርከን ውስጥ ያሉ ሰዎች ኃላፊነታቸውን ባአግባቡ ከመውጣት ይልቅ የግጭት ሃይሎችን ወደ ማጠናከር ሲሄዱ፤ ወይም ኃላፊነታቸውን ሆነ ብለው በመተው እነዚህ የግጭት ኃይሎች እንዲጠናከሩ እድል ሲሰጧቸው፤ የነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የኛ አይደሉም የሚሏቸውን ሰዎች (በብሔር፣ በሃይማኖት፣ … ወይም ሌሎችን ምክንያቶች ምክንያት በማድረግ) ሲያፈናቅሉ፣ ሲያሰድዱ፣ ሲያሰቃዩ፣ ሲከፋም ግድያዎችን ሲያስፋፉ ሰላም ጨርሳ ትጠፋለች።
ጠንካራ የውስጥ አሰራር አለመኖሩ(ወይም አስተዳደራዊ ድክመቶች) የሚያስከትላቸው ችግሮችን ዘርዝሮ መጨረስ ይከብዳል። የሰላም ባለቤት ህዝቡ ሲሆን ሰላም የሚሰፍነው ግን ህግ ሲከበር ነው። በሌላ በኩል የመንግስት ዋነኛ ኃላፊነት ህግን ማስከበር ነው። ህግን ለማስከበር በዋነኝነት የሰለጠነ እና በሰው ኃይል የተደራጀ የፍትህ ስርዐት ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ያለውን የፍትህ ስርአት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቢጠየቅ እንደማይተማመንበት መናገር ይቻላል። ህዝቡን መርዳትና መጠበቅ ያለበት ፖሊስ መንግስትን ይጠብቃል። ከሌባ ደግሞ የቤቱ አጥር ወይም በር ላይ የሚያስደግፋት ብረት ምጣድ ከፓሊስ የተሻለ ትጠብቀዋለች።
እንደሚታወቀው ፖሊስ እና ዳኛ፤ የፍትህ ስርአቱ የጀርባ አጥንት ናቸው። በመሆናቸውም እነሱን የተመለከት ማንኛውም ጉድለት ጥፋቱ ከፍተኛ ነው። ጥሩ ደሞዝ የሚከፈለውና በበቂ ሆኔታ የተማረ፣ የሰለጠነ፣ እና ህግ በሚፈቅድለት መልኩ ከመንግስት ትጽዕኖ ተላቆ በነፃነት የሚሰራ ፖሊስ ሳይኖር፤ በተመሳሳይ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ የዳኝነት ስርዐት ከሌለ ዝም ብሎ ሰላምን እንጠብቃለን ማለት ከንቱ ነው።
በሌላ በኩል በሀገሪቱ በስፋት የሚታየው ድህነት እና ስራ አጥነት በተለይ በወጣቱ ላይ የከፋ ነው። ለወጣቱ ምንም ገቢ ሳይኖረው ሲቀር ወይም ገቢው ለኑሮ በቂ ካልሆነ፤ ተስፋ መቁረጥ፣ ስራ ፈቶ ቁጭ ማለት እና ለሱስ ተጋላጭነት በወጣቱ ላይ ይንሰራፋል:: እናም የተለያዩ የግጭት ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች በቀላሉ የሚያማልሉት የወጣት ኃይል በስፋት እንዲኖር ያደረገዋል። ስለዚህ ሰላምን ለማስፈን የኢኮኖሚ ችግሮችን መፍታት አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም።
ለማጠቃለል ዘላቂ ሰላምን በሀገራችን ላይ ማስፈን የምንችለው፤ በህዝባችን የሚታመን ስርአት፣ እርስበርሳችን የመተባበር መንፈስ፣ እና ለሀገራችን ጥሩ የጋራ ራዕይ መፍጠር ከቻልን ነው።
በሃገራችን ብቅ ጥልቅ ያሉ የሰላም ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ከ17 አመት ጦርነት በኋላ ከ1984 እስከ 1988 እና ከ1992 እስከ 2015 የሚጠቀሱ አንፃራዊ የሰላም ጊዜያት ነበሩ። ግን እነዚያን የሰላም ጊዜያት ዘላቂ እና ቋሚ ማድረግ ተስኖን ቆይተናል።
ከሌሎች ሀገራት የምንማረው የኢኮኖሚ እመርታን መፍጠር የምንችለው ዘላቂ ሰላምን ካረጋገጥን ብቻ ነው። አንዴ እየሰራን ሌላ ጊዜ እየናድን በፍጹም አይሆንም።
ለዘላቂ ሰላም ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። እንደ አንድ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለች ሀገር መገንዘብ ያለብን ነገር ቢኖር ሰላምን ማረጋገጥ ለነገ የምንለው አይደለም። አሁኑኑ መጀመር ያለበን ጉዳይ ነው።